የሐይማኖት አባቶች የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐይማኖት አባቶች የሀገር ውስጥ ገቢን ለማሳደግ የጎላ ሚና እንዳላቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ከሐይማኖት አባቶች ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴም ባደረጉት ንግግር፤ መንግስት ለዜጎች የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማሟላት የሚችለው ከግብር በመሆኑ ዜጎች የግብር ግዴታቻውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ዜጎች ግዴታቸውን እንዲወጡም የሐይማኖት አባቶች ላበረከቱት የጎላ አስተዋጽኦ ተቋማቸው ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የሐይማኖት አባቶች ለግብር አሰባሰቡ ያላቸው ሚና በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ እና የቅዱስ ፓትሪያርኩ ተወካይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ እና ሌሎቹም የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል፡፡