Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የሚከበሩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ አዳዲስና ተጨማሪ በረራዎች ተጀምረዋል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የሚከበሩ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች አዳዲስና ተጨማሪ በረራዎች መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ እንደገለጹት፥ በክልሉ በታኅሣስ ወር መጨረሻ ቀናት እና ጥር ወር ላይ ለሚከበሩ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ በዓላት ዘርፈ ብዙ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በተለይም በዓላቱን ለማክበር ወደ ክልሉ ለሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ እንግዶች በቂ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በዚህ መሰረት ወደ ክልሉ የተለያዩ ከተሞች በዓላቱን ታሳቢ ያደረጉ አዳዲስ እና ተጨማሪ የአውሮፕላን በረራዎች መጀመራቸው ነው የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መርሐ ግብር እንደሚያመላክተው መጪዎቹን የጥምቀት እና ገና በዓላትን ምክንያት በማድረግ ከጎንደር-ላሊበላ፣ ከላሊበላ-ጎንደር እና ከባህር ዳር-ላሊበላ አዳዲስ በረራዎች ተጀምረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዓላቱን ታሳቢ ያደረገ ተጨማሪ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር እና ላሊበላ መፈቀዱ ተገልጿል፡፡

የገናን በዓል በላሊበላ፣ የጥምቀት በዓልን በጎንደርና ምንጃር ሸንኮራ፣ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓልን በእንጂባራ፣ የጊዮን በዓልን በሰከላ እንደዲሁም ጥርን በባህርዳር በክልሉ በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ናቸው፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.