Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርሕን ያከበረና ትብብርን የሚያጠናክር ነው – አምባሳደር ዲና

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርህን ያከበረና የቀጠናውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚደረግ ሙከራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደመገዳደር እንደሚቆጠርም ጠቁመዋል፡፡

ስምምነቱ የህዝቦችን በትብብር ማደግ የሚያረጋግጥና ማንንም የማይጎዳ ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ህዝብና በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗንና በተለይ የኢኮኖሚ እድገቷ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም የወደብ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ህልውና መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታከናውነው የትኛውም ሰላማዊ ጥረት በመልካም ሊወሰድና የትኛውም አካል ሊደግፈው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት ከድህነት ለመውጣት የሚደረግ ጥረትና ከብሔራዊ ጥቅም ጋር እንደሚተሳሰር አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚደረግ ሙከራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደመገዳደር እንደሚቆጠር ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበሩ ስራ ደግሞ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ ማስረዳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቀጣናው የሚደረግ የኢኮኖሚ ትብብር የሰላም እንጂ የግጭት ምንጭ እንደማይሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.