Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት ከጥር 2 እስከ 24 ይካሄዳል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ” በሚል መሪ ሐሳብ የዲፕሎማሲ ሳምንት ከጥር 2 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ የዲፕሎማሲ ሳምንት መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ፣ አሁን የደረሰበትን እና የቀጣይ ስራን የሚያሳዩ ፕሮግራሞች መካተታቸውን ገልጸዋል።

የዲፕሎማሲ ሳምንቱ ኢትዮጵያ በዓለም ተቋማትና ድርጅቶች መመስረትና በመምራት ያላትን የገዘፈ የዲፕሎማሲ ታሪክም ለማሳየት ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ በማሳየት በአፍሪካ ቀንድ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የተጫወተችውን ሚና ማሳየት አንዱ ዓላማ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የባለብዙ ወገንና ሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስኬትና ተግዳሮቱን በማሳየት ህብረተሰቡ ደጋፊ እንዲሆን ማስቻል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ ታሪክና አቅም አውቆና ተረድቶ ድጋፍ እንዲያደርግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ለሶስት ሳምንት በሚቆየው መርሐ ግብር ከአፍሪካ መዲና እስከ አለም መድረክ በሚል መሪ ሃሳብ አውደርዕይ፣ የፓናል ውይይት እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ116 አመት ጉዞ የሚያሳይ መጽሐፍ ለአንባቢያን መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ስድስት ጥናታዊ ጽሑፎች በባለሙያዎችና ምሁራን እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን÷ ዲፕሎማቶችን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድርም ይካሄዳል ተብሏል፡፡

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ ከመንግሥታቱ ማኀበር እስከ ብሪክስ አባልነት የተጓዘችበትን የዲፕሎማሲ መንገድም እንደሚያሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.