የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ፀጉርና ከመቅደላ የተወሰዱ ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ ፀጉር እና በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ጦር የተወሰዱ ታሪካዊ ቅርሶች ተመለሱ።
የተመለሱት ታሪካዊ ቅርሶች ሁለት በብር የተለበጡ ዋንጫዎች፣ አንድ የቀንድ ዋንጫ፣ ደብዳቤዎች እንዲሁም አንድ ጋሻ ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ቅርሶቹን ይዘው እንደተመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለቅርሶቹ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው(ረ/ፕ) አቀባባል እንዳደረጉም ተገልጿል፡፡
ቅርሶቹን ማስመለስ መቻሉ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑንም አምባሳደር ተፈሪ ተናግረዋል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴና ሼኸራዛድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባለፈው መስከረም ቅርሶቹን ማስመለሳቸው ይታወሳል።
መንግስት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው በተለያዩ ሀገራት ሙዚየም የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚያደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል፡፡