Fana: At a Speed of Life!

“የስማርት ኮርት” ስርዓት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በልፅጎ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ስርዓቱን በማቀላጠፍ እና ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ትልቅ ድርሻ ይጫወታል የተባለለት “የስማርት ኮርት” ስርዓት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በልፅጎ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተላልፏል።

በውስጡ አራት መተግበሪያዎች ያሉት የስማርት ኮርት የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ በማድረግ የፍትሕ ስርዓቱን የሚያሻሽል ይሆናል ተብሏል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የበለፀገውን የስማርት ኮርት መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል።

የስማርት ኮርቱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎቱን ወረቀት አልባ እና ኢ ፍርድ ቤት ለመገንባት እየሰራቸው ካሉ ስራዎች አንዱ መሆኑም ተገልጿል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ እንዳሉት÷ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎቶች የዜጎች ዋስትና በመሆኑ አገልግሎቶቹን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ ሊደገፉ ይገባል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያበለፀገው መተግበሪያም የዳኝነት አሰጣጡን ቀልጣፋ በማድረግ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው÷ ለሕግ የበላይነት መከበርና ለፍትህ መስፈን ፍርድ ቤቶች የተቀላጠፈ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.