Fana: At a Speed of Life!

የዳራሮ በዓልን አልምቶ ለቱሪዝም መስህብነት ማዋል ይገባል – አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓልን ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በማልማት ለቱሪዝም መስህብነት ማዋል እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

ዳራሮ በዓል ” ክብር ለአርበኛ አርሶ አደሮቻችን ዳራሮ ለአንድነታችን ” በሚል መሪ ሃሳብ በዲላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በወቅቱ እንዳሉት÷ ዳራሮ ከዘመን መለወጫነቱ በተጓዳኝ በበርካታ ጠቃሚ እሴቶች የታጀበ ህዝባዊ መሠረት ያለው በዓል ነው።

በተለይ የጌዴኦ ባህላዊ የአካባቢ ጥበቃ ባህል ሰውና ተፍጥሮን በማስተሳሰር ድንቅ እሴት መሆኑን በመገንዘብ ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በዓሉ በይበልጥ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲጎለብት በዞኑ ከሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች ጋር በማስተሳሰር መስራት ይገባል ሲሉም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

የለውጡ መንግስት ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብቶች ለይቶ በማልማት ቱሪዝም ቀዳሚ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዳራሮን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለመስህብ ሃብቶች የሚውል እምቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰው÷ ይህንን በመጠበቅና በማልማት ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ የቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አምባሳደር ናሲሴ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዳራሮ በዓል ከዘመን መለወጫነት ባሻገር ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚጎላበት የፍቅርና የመቻቻል በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪና የርዕሰ መስተዳድሩ ተወካይ አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።

ይህንን ውብ በዓል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ብሎም በይበልጥ እንዲጎለብት በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.