አቶ እንዳሻው ጣሰው በበጋ ወቅት መደበኛ መስኖ 70 ሺህ ሔክታር መልማቱን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጋ ወቅት በመደበኛ መስኖ 450 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 70 ሺህ ሔክታር በአትክልትና ፍራፍሬ መልማቱን የክልሉ ም/ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡
በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ም/ርዕሰ መሥተዳድሩ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ባቀረቡት ሪፖርትም ክልሉ ከተቋቋመ ጀምሮ÷ ለዓመታት የቆዩ ልዩ ልዩ የልማትና መልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መመለስን ጨምሮ የዜጎች አገልግሎትና መሰረታዊ መብቶችን የሚያሟላ ሰባት የክልል ማዕከላት አደረጃጀትን መፍጠርና ማጠናከር መቻሉን አንስተዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍም በመኸር ወቅት ከ491 ሺህ ሔክታር በላይ በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው፤ አብዛኛው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የለማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከ185 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸው÷ በ30-40-30 እና በመደበኛ ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 8 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኞች መተከሉን አመላክተዋል፡፡
በመኸር ወቅት በሁሉም አዝርእት፣ አትክልትና ፍራፍሬ በዘር ከተሸፈነው 491 ሺህ 846 ሔክታር ከ30 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
በ2016 የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም 11 ሺህ 230 ሔክታር ለማልማት ታቅዶ እስከ አሁን 3 ሺህ 500 ሔክታር የሚጠጋ መሬት መዘጋጀቱን እና ከ1 ሺህ ሔክታር በላይ መልማቱን አንስተዋል፡፡
በዚህ ልማት 4 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በክልሉ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የቅመማ ቅመም ምርት መመረቱንም አስታውቀዋል፡፡