Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ በቱሪዝም ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በቼክ ሪፐብሊክ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጉብኝቱ በኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ መካከል እየተጠናከረ የመጣውን የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በቱሪዝም ዘርፍም ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ሚኒስትሯ ከቼክ ሪፐብሊክ ባህል ሚኒስትር ማርቲን ባክሳ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች ወደ ተግባር ለመቀየር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚህም መሰረት በአቅም ግንባታ መስክ፣ ብሄራዊ ሙዚዬሞችን ለማዘመን በሚደረገው ጥረትና የተለያዩ የሙዚዬም ስብስቦችን በጊዜያዊ ኤግዝቢሽን መልክ በልውውጥ በየሀገራቱ ለማሳየትና አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ከቼክ ሪፐብሊክ ብሄራዊ ሙዚዬም ዳይሬክተር ጀነራል ሚካኤል ሉኬስ እና ከዲቩር ክራሎቬ ሳፋሪ ፓርክ ዳይሬክተር ፕሪሚስል ራባስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በዱር እንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ፣ በዘርፉ የሚደረግ ጥናትና ለአደጋ ለተጋለጡ የዱር እንስሳት መጠለያ ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.