የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ለጉብኝት ክፍት ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለጉብኝት ክፍት እንደሚደረግ የድል መታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር ውባየሁ ማሞ (ኢ/ር) ገለፁ ።
የጉብኝቱን ሒደትና የሚጎበኙ ሥፍራዎችን በተመለከተ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም መግለጫ እንደሚሰጥም ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቀዋል፡፡
ከ128 ዓመታት በኋላ ለዓድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በመሃል ፒያሳ የተገነባው ይህን ግዙፍ መታሰቢያ የካቲት 3 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት በይፋ መመረቁ ይታወሳል።
እስካሁንም የአፍሪካ መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት ጎብኚዎች የድል መታሰቢያውን እንደጎበኙ ነው የገለጹት።
ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲጎበኘው ይደረጋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የፊታችን ዓርብ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመደበኛ እና ለልዮ ጎብኚዎች የተቀመጠው የክፍያ መጠን ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።