ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ የሚያደርጉትን ውይይት ለመቀጠል ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ የሚያደርጉትን ውይይት ለመቀጠል መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ በዴሚን ሙርፊ የተመራ ከፍተኛ የባለሞያዎች ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ÷ መንግሥት የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን በመንግሥት በኩል በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሰላም ግንባታ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እና እየተሰሩ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል፡፡