Fana: At a Speed of Life!

የሰራተኞችን መብትና ጥቅም የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሰላምን የማረጋገጥ፣ ምርታማነትን የማሳደግ፣ የሥራ ላይ ደህንነትንና የሰራተኞችን ጥቅም የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የዓለም የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ49 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135 ጊዜ “ለሠላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንሻለን” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ በተከናወነው መርሃ ግብር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሰራተኛ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የሰራተኞችን ጥቅምና መብቶች የማስከበር እንዲሁም ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የሰራተኛውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ በሂደት ምላሽ ለመስጠትም አሰራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሠራተኞችን መብትና ጥቅም በዘላቂነት ለማስጠበቅም አዳጊ ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገ ሪፎርም ተሰርቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው፤ ሰራተኞች የላቀ እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸውም በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሣሁን ፎሎ፤ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ከመንግሥት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.