Fana: At a Speed of Life!

ከደንበኞች ዕውቅና ውጭ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ወስዷል የተባለ ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ከተለያዩ ደንበኞች ዕውቅና ውጪ ወስዷል የተባለ ግለሰብ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ከፍተኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

ተከሳሽ ሚካኤል ታዬ በቀለ በአዋሽ ባንክ አ.ማ መሳለሚያ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ሆኖ በሚሠራበት ወቅት ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የተሰጠውን ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ያለ አግባብ በመገልገል የባንክ ብራንች ኦፕሬሽን እና ካሽ ማኔጅመንት ፕሮሲጀር ማኑዋል አንቀጽ 6 እና አንቀጽ 7.5 ንዑስ አንቀጽ (1) ሀ፣ ለ እና ሐ ላይ የተዘረዘሩትን በመጣስ፣ ከባንኩ ደንበኞች ዕውቅና ውጭ የደንበኞችን ፊርማ አመሳስሎ በመፈረም እና ደንበኞቹን አጭበርብሮ እንዲፈርሙለት በማድረግ፣ ቋሚ ደንበኛ በባንኩ መመሪያ መሰረት መታወቂያ እንዲያቀርቡ ስለማይገደዱ የገንዘብ ማስተላለፍያ ፎርሙ ላይ “Regular Customer or Known to Me” የሚል ጽሑፍ መጻፉ በክስ መዝገቡ ላይ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ከእሱ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ላይ የሚገኙትን የባንኩን ሠራተኞች ደንበኞቹ ወረፋ ስለሆነባቸው የወጪ ማዘዣው ላይ እና የማስተላለፊያ ፎርሙ ላይ ፈርመው እንዲሄዱ ማድረጉም በክሱ ተመላክቷል፡፡

ተከሳሹ ከባንኩ ደንበኞች ዕውቅና ውጪ 1 ሚሊየን 781 ሺህ 316 ብር ከ25 ሣንቲም ወጪ ማድረጉ፣ ወደ ሌላ አካውንት ካስተላለፈ በኋላም ወደ ቴሌ ብር እና ሞባይል ባንኪንግ በመላክ መውሰዱ እንዲሁም ያስወሰደ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በዚህም መሠረት የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) ሀ እና (2) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ፤ በፈጸመው ስልጣንን ያለ አግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን በ5 ዓመት ጽኑ እስራትና በ4 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡

በመቅደስ የኔሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.