በኢንዱስትሪውና በምርት ፈላጊው መካከል የአቅርቦት ሰንሰለትን በማጠናከር ልማትን ማፋጠን ይገባል- ም/ጠ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪውና በምርት ፈላጊው መካከል የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማጠናከር ልማትን ለማፋጠን መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የልዑካን ቡድን በባህር ዳር ከተማ የልማት እንቅስቃሴዎች ተመልክቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማትና በሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
በከተማዋ ያለው የእንስሳት መኖ ማምረቻ ፋብሪካ ለእንስሳት ማድለብ፣ ለወተት ላሞች፣ ለዶሮ፣ ለግመልና ሌሎች እንስሳት የሚውል መኖ በብዛት እየተመረተ እንደሚገኝ በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የእንስሳት አርቢዎች ለሚያነሱት የመኖ አቅርቦት መሰረታዊ ጥያቄ መመለስ እንደሚቻል መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል የሚስተዋለውን ክፍተት ለመሙላት የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች ከፋብሪካው የመኖ ምርት የሚወስዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ለማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት መስጠቱን የገለጹት ደግሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ናቸው።
በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች በስፋት በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሰፊ የስራ እድልና የእውቀት ሽግግር በመፍጠር ዘላቂ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማትና በግብርና ላይ ያተኮረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የማይነጣጠሉ የሀገር እድገት መሰረት ናቸው ብለዋል።
ግብርናው ለኢንዱስትሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎች ለገበታ ለሀገር ግብዓት በማቅረብ ተመጋጋቢ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታም ምርቶችን በፍጥነት ለማድረስ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማዋና አካባቢው ያለው ሰላም ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ በማምረትና ሌሎች ስራዎች በማከናወን ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።