በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ‘ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት’ በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ÷ በዞኑ 23 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሥራ ዕድል እየፈጠሩና የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚቀንሱና የሚያስቀሩ ተኪ ምርት በማምረት አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ እንዳልካቸው ጌታቸው (ዶ/ር)÷ መንግስት የሀገራዊ ኢንዱስትሪ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቀየስ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ ለዘርፉ ትኩረት በመሰጠቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው÷ 74 ነባር ኢንዱስትሪዎች ተለይተው ተገቢው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
በክልሉ ከሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን ዘርፉን ለመደገፍ አደረጃጀት መፈጠሩንና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የኢንዱስትሪ አቅም ልየታና አዋጭነት ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 49 አዳዲስ ባለሀብቶች በዘርፉ መሰማረታቸውን ገልጸው÷ በቀጣይም በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዞን 54 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
ዘርፉ የስራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነም አመላክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባዉዲ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጥሮ ሀብታችንን ሳንጠቀም ቆይተናል በማለት ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሁሉን አቀፍ ጥረት መጀመሩን ተናግረዋል።
በማቱሳላ ማቴዎስ