Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕውቀት መመራት ይጠበቅበታል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕውቀትና በዕቅድ መመራት እንደሚጠበቅበት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ሸዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ከጎበኙ በኋላ ከአልሚ ባለሃብቶችና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግርም በተፈጥሮ ያለንን ዕምቅ ዐቅም በመጠቀም መሥራት ከቻልን ሀገርን የመለወጥ ዐቅም በእጃችን ነው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በዕውቀትና በዕቅድ መመራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበው÷ መሬትን ሳያለሙ አጥረው በሚያስቀምጡ አካላት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ ባለሃብቶች ቢስተካከሉ ተብለው የተነሱ ጉዳዮችን ክልሉ ለማስተካከል ይሠራል ብለዋል፡፡

በቡልጋ ከተማ ከ46 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 208 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸው እና ከ18 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውም በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በሰሜን ሸዋ ዞን ከ174 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ2 ሺህ 375 በላይ ባለሃብቶች ፈቃድ መውሰዳቸውን እና ከ39 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውም ተገልጿል።

በኤልያስ ሹምዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.