ዓለም ባንክ የገቢ ማሻሻያ ተግባራት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ባንክ የትኩረት መስክ ተብለው የተለዩ የገቢ ማሻሻያ ተግባራት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡
በዓለም ባንክና ገቢዎች ሚኒስቴር መካከል ሀገራዊ የገቢ ማሻሻያ ተግባራት የተሳኩ እንዲሆኑ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ሀገራዊ ገቢን በማሳደግ የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት በሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት 25 የገቢ ማሻሻያ ተግባራትን ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱም ነው የተጠቆመው፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የስራ ኃላፊዎች በሚኒስቴሩ ተገኝተው ዛሬ የተደረገው ውይይት የገቢ ማሻሻያ ተግባራትን በሚፈለገው ደረጃ ተፈጻሚ ለማድረግ እየተወሰደ ላለው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
በመድረኩም የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፥ ከታክስ አሰባሰብና አስተዳደር አንፃር እንደሀገር በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ዓለም ባንክ በተለይም እንደ ተቋም የትኩረት መስክ ተብለው የተለዩ የገቢ ማሻሻያ ተግባራት ዙሪያ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የታክስ አሰባሰቡ ከተቀመጠው ዓመታዊ ግብ አንፃር የተሳካ ነው ሊባል የሚችል ቢሆንም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀገራዊ ሀብት እንዲሁም ከሠሃራ በታች ካሉ ሀገራት ገቢ አንፃር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም አብራርተዋል ሚኒስትሯ፡፡
ከግብር አሰባሰብ፣ ከግብር ከፋዮች አገልግሎት፣ ከዲጂታላይዜሽን፣ ከሰው ኃይል አስተዳደርና አቅም ግንባታ አንፃር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የዓለም ባንክ ልኡካን ቡድን አባላቱም የገቢ ማሻሻያ ተግባራቱን ለመደገፍ መስማማታቸውን ገልጸው፥ የሚደረገው ድጋፍ የተቋሙን የአሰራር ሂደት ተከትሎ እንደሚከናወን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡