ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሩሲያ እየተካሄደ በሚገኘው ኢኮኖሚያቸው በማደግ ላይ ያሉ የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ኢትዮጵያን በመወከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ስብሰባው ፥ ቡድኑ ከአምስት አባላት ወደ ዘጠኝ ማለትም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራንና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በይፋ ከተቀላቀሉ በኋላ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።
በመድረኩ ቱርክን ጨምሮ ሌሎች 15 ሀገራት መጋበዛቸውንም የብሪክስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡
ስብሰባው ባሳለፍነው ወር በሄሊኮፕተር አደጋ ለሕልፈት የተዳረጉትን የኢራን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር አብዶላሂን በማሰብ በህሊና ጸሎት ተጀምሯል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ፥ ባለፈው ዓመት በጆሃንስበርግ በተደረገ የብሪክስ ስብሰባ ላይ የተደረሱ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም አባል ሀገራቱ በራሳቸው ገንዘብ መገበያየትንና ሌሎች ውሳኔዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡