የሐረሪ ክልል ያልተገባ ክፍያ በሚጨምሩ ት/ቤቶች ላይ ርምጃ እወስዳለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመመሪያ ውጭ ያልተገባ የትምህርት ቤት ክፍያ በሚጨምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በ2017 የትምህርት ዘመን ከትምህርት ቤት ክፍያ ጋር ተያይዞ ጭማሪ ያደረጉና ያላደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን የቢሮው ኃላፊ ጌቱ ነገዎ ተናግረዋል፡፡
ከግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች ጋር በተደረገ ውይይትም ከመመሪያ ውጭ ያልተገባ ክፍያ ማድረግ እንደማይቻልና ጭማሪ ሲደረግም ከሚያዝያ 30 በፊት ወላጆችን በማወያየት በቃለ-ጉባዔ ማቅረብ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
16 የግል ትምህርት ቤቶች ከሚያዝያ 30 በፊት አሳማኝ ምክንያታቸውን ለወላጆች በማቅረብና ስምምነት ላይ በመድረስ መጠነኛ ጭማሪ ማድረጋቸውንም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች መመሪያው ከሚያዘው ውጭ በወላጆች ላይ ጫና የሚፈጥር የተጋነነ የክፍያ ጭማሪ ስለማድረጋቸው መረጃ አለን ብለዋል፡፡
መመሪያውን ተላልፈው ጭማሪ በማድረግ ሕብረተሰቡን በሚያማረሩ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ፈቃድ እስከ መንጠቅ የሚደርስ ርምጃ እንወስዳለን ብለዋል፡፡
በአንፃሩ 16 የግል ትምህርት ቤቶች የወቅቱን ሁኔታ በማገናዘብና “ጭማሪ ብናደርግ ሕዝቡ ይቸገራል” በማለት ጭማሪ አለማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
በቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ዳዊት ለገሰ እንዳሉት÷ 6 ትምህርት ቤቶች ከወላጅ ጋር ምንም ዓይነት ውይይት ሳያደርጉ እንዲሁም 14 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ቀነ ገደቡ ካለፈ በኋላ ውይይት አድርገናል በማለት የተጋነነ የክፍያ ጭማሪ ማድረጋቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህም ከመመሪያው ውጭ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡