Fana: At a Speed of Life!

ለአልሸባብ ድጋፍ በማድረግና መረጃ በማቀበል ወንጀል የተከሰሱ 9 ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአልሸባብ የሽብር ቡድን የጦር መሳሪያ መሬት ውስጥ በመደበቅ፣ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እና መረጃ በማቀበል ወንጀል የተከሰሱ ዘጠኝ ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ የሽብር ወንጀል ተግባር ሲፈጽሙ በጸጥታ አካላት የተያዙ 84 የአልሸባብ የሽብር ቡድን ወታደሮች ላይ የዓቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ብይኑን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ ጅግጅጋ ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ነው።

ተዘዋዋሪ ችሎቱ በነ ሙክታር አብዲ አሊ መዝገብ የተካተቱ 84 የአልሸባብ ወታደሮችን የክስ መዝገብ እንዲሁም አበሽር አህመድ መሃመድ እና ሻለቃ ሀለኒ ኑርዬ በተባሉ መዝገቦች የተካተቱ የ9 ግለሰቦችን የክስ መዝገብ ተመልክቷል።

ተከሳሾቹ በ2014 ዓ.ም መጨረሻ በተሳተፉበት የሽብር ወንጀል ተግባር ላይ እያሉ በኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊትና በሶማሌ ክልል የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መርማሪዎች ምርመራ ተደርጎባቸው በዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ዓቃቤ ሕግ በነ ሙክታር አብዲ አሊ መዝገብ በተካተቱ 84 ተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1 ሀ እና ለ አንቀጽ 35 እንዲሁም ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት የተሳትፎ ደረጃቸው ተጠቅሶ ዝርዝር የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ እነዚሁ 84 ተከሳሾች የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት የተፈረጀው አልሸባብ የሽብር ቡድን ድርጅት አባል በመሆን የወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ መቀመጫውን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ያደረገው የአልሸባብ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባል በመሆን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠና በመውሰድ፣ ህዝብን በማሸበር መንግስትን ለማስገደድ የተሰጣቸውን ተልኮ ተቀብለው ከሐምሌ 12 ቀን እስከ ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በሶማሌ ክልል አፍዴር ዞን እና በሸበሌ ዞን በቱያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በሚገኙ አካባቢዎች የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ማለትም ላውንቸር፣ብሬን ስናይፐር እና ቦምብ በመታጠቅ ተኩስ በመክፈት ጥቃት መፈጸማቸው በክሱ ተመላክቷል።

በተፈጸመው ጥቃትም የ265 ዜጎችን ሕይወት በማጥፋት የ323 ንፁሃንን እና የቀድሞ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት እንዲሁም አካባቢውን በሚጠብቁ ሚሊሻዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት በማድረስ እንዲሁም 13 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህዝብ መገልገያ ንብረቶች ላይ ጉዳት በማድረስ ከ500 በላይ ፍየሎችና ግመሎችን መዝረፋቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

እነዚህ 84 ተከሳሾች በተዘዋዋሪ ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝር እንዲደርሳቸው ከተደረጉ እና ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ የክስ ዝርዝር ላይ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት “አልፈጸምንም” በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ ምስክሮች እንዲሰሙለት ባቀረበው ጥያቄ መነሻ ተዘዋዋሪ ችሎቱ የ11 ምስክሮችን ቃል ካዳመጠ በኋላ የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመስማት ለሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ተዘዋዋሪ ችሎቱ በሽብር አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 2 የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ለሽብር ቡድኑ የተያዩ የጦር መሳሪያዎችን በኤልኬሬ ወረዳ በደው ቀበሌ መሬት ውስጥ ቀብረው በጸጥታ አካላት ኦፕሬሽን የተገኙ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

እንዲሁም ተከሳሾቹ የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሽብር ተግባር ላይ ተሳትፈው እያለ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በመጥቀስ ዓቃቤ ሕግ በእነ አበሽር አህመድ መሃመድ መዝገብ የተካተቱ 4 ሰዎች ላይ ክስ አቅርቦባቸዋል።

ሌሎች በእነ ሻለቃ ሀለኔ ኑርዬ ኡመር መዝገብ የተካተቱ 5 ሰዎች ደግሞ ለአልሸባብ የሽብር ቡድን በገንዘብ ድጋፍ በማድረግና መረጃ በማቀበል የሽብር አዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 /ሀ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው የተከሰሱ ናቸው።

እነዚህ በሁለት መዝገብ ጉዳያቸው የታየላቸው አጠቃላይ 9 ግለሰቦች የቀረበባቸውን ክስ በየደረጃው ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ ዓቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦባቸዋል።

ተዘዋዋሪ ችሎቱም የዓቃቤ ሕግን ምስክር ቃል በመመርመር ወንጀሉ መፈጸሙን በዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ማረጋገጡን ጠቅሶ እያንዳንዳቸው በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ተከላከሉ የተባሉ እነዚህ 9 ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ተዘዋዋሪ ችሎቱ ለመጠባበቅ ለሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.