ኢጋድ ለኢትዮጵያ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ የድርጊት መርሐ ግብር ግምገማ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
የግምገማ መድረኩን ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን በመተባበር ነው ያዘጋጁት፡፡
ብሉ ኢኮኖሚ በውሃማ አካላት ላይ የሚደረጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ስትራቴጂ በመምራት ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ማዋልን ማዕከል ያደረገ የልማት ዘርፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢጋድ የአካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ፕሮግራም ሃላፊ እሸቴ ደጀኔ (ዶ/ር) እንዳሉት÷የኢጋድ አባል ሀገራት በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ሃብት እንዲጠቀሙ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ አዘጋጅታ በማጽደቅ ለስትራቴጂው ትግበራ በርካታ ሥራዎች እያከናወነች እንደምትገኝ አንስተዋል።
ኢጋድ ለኢትዮጵያ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ የውቅያኖስ፣ የሐይቅ፣ የባህርና ሌሎች ተያያዥ ሃብቶቿን በአግባቡ እንድትጠቀም ያስችላታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዘርፉ ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላት ጠቁመው÷ይህን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የባለስልጣኑ የማሪታይም አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ ካፒቴን ጌትነት አባይ÷ ለብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ መሳለጥ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በእያንዳንዱ ተቋም ለስትራቴጂው ትግበራ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በትብብር እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን÷የኢትዮጵያን ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራን እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጧል።