Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች ከለላና ድጋፍ እያደረገች መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች ከለላና ድጋፍ እያደረገች መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬከተር ጠይባ ሀሰን÷ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችን እያስተናገደች ቢሆንም ዜጎቿ ደግሞ በህገ ወጥ ስደት ለችግር እየተዳረጉ በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።

ከተለያዩ ሀገራት መንግስታት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይት በማድረግ መንግስት ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት እየመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ26 ሀገራት የገቡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ፍልሰተኞችን ተቀብላ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በአግባቡ እየፈጸመች ትገኛለች ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች፣ ድህነትና ስራ አጥነት ህገ ወጥ ስደትን እያባባሱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ፍልሰተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ ትብብር ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬከተሯ÷ አሁን ያለው ትብብርና ድጋፍ እየቀነሰ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ለጋሽ ሀገራትም በጦርነትና መሰል ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል በቂ ሃብት ለመመደብ መቸገራቸውን እየገለጹ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህ ሳቢያም በኢትዮጵያ ለስደተኞች ድጋፍ ከለጋሾች የሚገኘው ሀብት ውስን በመሆኑ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፋዊ ትብብር እንዲደረግ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.