በአርባ ምንጭ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርባ ምንጭ ከተማ “ስቴይ ግሪን አርባ ምንጭ” በሚል መሪ ሃሳብ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ፡፡
ሩጫው በተለያዩ የዕድሜ ደረጃዎች እየተካሄደ ሲሆን÷ 800 ሜትር የህፃናት ውድድር አስቀድሞ ተካሂዷል።
መነሻውንና መድረሻውን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አደባባይ ያደረገው የ7 ኪሎ ሜትር የአዋቂዎች ሩጫ ውድድርም ተካሂዷል።
ውድድሩ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረና በዘርፉ ግንዛቤ ማስጨበጥን አላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የፕላስቲክና የወረቀት አጠቃቀምን በመቀነስ ሃላፊነት የተሞላበት የቆሻሻ አወጋገድንና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለመስራት ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ አክሊሉ ታደሰ÷መንግስት የስፖርት ቱሪዝም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስፖርታዊ ውድድሮች ባህልን፣ ተፈጥሮን እና ታሪክን ከማስተዋወቅ ረገድ ለሀገር መልካም እድሎች የሚፈጥሩባቸው መድረኮች እንደሆኑም ገልዋል።
የሀገር ውስጥ ቱሪስት መስሕቦችን በማስተዋወቅ የውስጥ ኢኮኖሚ ምንጭን ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በማቴዎስ ፈለቀ