የብልጽግና ፓርቲ የ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ በዋና ጽ/ቤት እና በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ የፓርቲ ስራዎች የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ በም/ጠ/ሚ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽ/ቤትና የቅርጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
መርሐ ግብሩን በንግግር የከፈቱት አቶ አደም ፋራህ÷ውይይቱ የዓመቱን አፈጻጸም ጥንካሬዎች በመለየት ለቀጣይ አቅም አድርጎ ለመጠቀም ያለመ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በክፍተት የታዩ ጉዳዮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ የሚቻልበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ፓርቲው ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት እና የእቅዶችን አፈጻጸም ለመገመገም የተካሄዱ የሱፐርሲዥን ሥራዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም የፓርቲ የተለያዩ የአሠራር ስርዓቶችን ወጥ ለማድረግ የተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡