የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ላበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጠው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለመግታት በተደረገው ዓለም አቀፍ ርብርብ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጠው፡፡
አየር መንገዱ በካናዳ ቶሮንቶ በተካሄደ የመጀመሪያው ድህረ ኮቪድ ኮንፈረንስ ላይ ነው የዕውቅና ሽልማት የተበረከተለት፡፡
ሽልማቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በአፍሪካ እና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ሀገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ጥቅም ላይ ያዋሉዋቸውን የተለያዩ የሕክምና ቁሳቁሶች በማጓጓዝ የተቀላጠፈ አገልግሎት ሰጥቷል።
በዚህም የበርካቶችን ህይወት ለመታደግ በተደረገው ጥረት ለነበረው የጎላ ሚና ዕውቅናና ሽልማት የተሰጠው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኮንፈረንሱ የተዘጋጀው በዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል ኢኒሼቲቭ፣ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የተለያዩ ወረርሽኞችን በጋራ መከላከል ላይ አተኩረው በሚሰሩ የሥራ አጋሮች ትብብር መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል፡፡