Fana: At a Speed of Life!

አርመኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአርመኒያ አምባሳደር ሳህክ ሳርግስያ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ሀገራቱ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትብብር መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር )÷ ኢትዮጵያ ለሳይንስ፣ ቴከኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሀገራዊ ኢኮኖሚውን እድገት ለመቀየር ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማበልፀግ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት ከአርመኒያ እና ከሌሎች በዘርፉ ልምድ ካላቸው ሀገራት ጋር የጠበቀ ትስስር መፍጠር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በዚህም በተመረጡ እና ለህዝቦች እድገት አጋዥ የሆኑ ጉዳዮችን በማፈላለግና ወደ ውጤት የመቀየር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

አምባሳደር ሳህክ ሳርግስያን በበኩላቸው÷ ከኢትዮጵያ ጋር በአይሲቲ፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪ እና በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የምትሰራቸውን የትብብር ሥራዎች ከሁሉም ቅድሚያ ትሰጣለች ያሉት አምባሳደሩ÷ በኢትዮጵያ ሰፋፊ ሥራዎችን በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

በሀገራቱ መካካል የነበሩ ስምምቶችና ውይይቶችን በማጎልበት አስፈላጊ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ወደ ተግባር እንደሚገባ መጠቆሙንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.