የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ ተማሪዎች 97 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ፈተናውን ወስደዋል- ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል 97 ነጥብ 5 በመቶው ፈተናውን መውሰዳቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) የዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና መጠናቀቅን ተከትሎ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ በመላ ሀገሪቱ የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 701 ሺህ 749 ተማሪዎች መካከል 97 ነጥብ 5 በመቶው ፈተናውን ወስደዋል ብለዋል።
ቀሪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን ዘግይተው በመጀመራቸው ፈተናውን እንዳልወሰዱ ነው የገለጹት፡፡
የትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መልቀቂያ ፈተና ዛሬ ጠዋት መጠናቀቁን የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷ ፈተናው በመላ ሀገሪቱ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 29 ሺህ 718 ተማሪዎች በበይነ መረብ የተፈተኑ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የበይነ መረብ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠቱን ጠቅሰው÷ በቀጣይ ለሚሰጠው ፈተና የተሻለ ተሞክሮ የተገኘበት ነውም ብለዋል።
በፈተናው ሒደት ተማሪዎች በፈተና ወቅት እንዳይዙ የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ቀዳሚ ችግር እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በፈቲያ አብደላ