የኮሪደር ልማቱ በህዝብ ተሳትፎ ልማትን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን እንደሚቻል ማሳያ ነው – ወ/ሮ ሎሚ በዶ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በህዝብ ተሳትፎ ልማትን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን እንደሚቻል ጥሩ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ም/ አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴት ኮከስ አባላት የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል።
ም/አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት በአመራሩ ቅንጅትና በህዝብ ተሳትፎ ልማትን በፍጥነትና በጥራት ማከናወን እንደሚቻል ጥሩ ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት ነው።
ለሀገር ገጽታ ግንባታና ለዜጎች የተሻለ የአኗኗር ሒደት ጥሩ መሰረት ያኖረ መልካም ጅምር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው÷ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት የአመራሩና የህዝቡ የጋራ ትብብር ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
የመዲናዋን ገፅታ በመለወጥ ለኑሮ ምቹና ውብ ከማድረግ ባለፈ ሁነኛ ተመራጭ የቱሪስ መዳራሻ ከተማ የሚያደርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ዝናሽ ፀጋየ÷ የኮሪደር ልማቱ የአዲስ አበባን ገጽታ ያስዋበና ለኑሮ ምቹ ያደረገ መሆኑን በጉብኝታችን ተመልክተናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለጎብኝዎቹ በሰጡት ገለፃ÷ የኮሪደር ልማቱ ሁሉንም የመሰረተ ልማት በማካተት በህዝብ ተሳትፎ በጥራትና በፍጥነት የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በትብብርና በትጋት መስራት ከተቻለ የሀገርን እድገትና የዜጎችን ሕይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ እንደሚቻል ልምድና ተሞክሮ የተገኘበት ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።