ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኩባ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሊዮ ኢድዋርዶ የተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ ኩባ ለኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በትምህርት፣ በንግድ፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በውሃ አስተዳደር እና ሌሎች ዘርፎች ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ኢሊዮ ኢድዋርዶ በበኩላቸው÷ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በትብብር ለመስራት ሰፊ አቅም መኖሩን ገልጸው÷ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ የፖለቲካ ምክክር ስምምነት መፈራረማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡