በተከዜ ወንዝ በጀልባ ተሳፍረው ሲጓዙ የነበሩ 12 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋግ ኸምራ ብሔረ-ሰብ አስተዳደር ከሰሃላ ሰዬምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጎዙ የነበሩ 12 ሰዎች በድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
መነሻቸውን ሰሃላ ሰዬምት ወረዳ መሸሃ ከተማ እና ሰላዝጌ ቀበሌ አድርገው ወደ ዝቋላ ወረዳ ሀገረ- ሰላም ቀበሌ ዘመቁ ደብር ቀብር ለመድረስ ሲጓዙ የነበሩ 26 ሰዎች በጀልባ ተሳፍረው ተከዜ ወንዝን አቋርጠው በመጓዝ ላይ እያሉ ድንገት በተፈጠረ የጎርፍ አደጋ ነው የ12 የሰዎች ሕይወት ያለፈው፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ÷እስካሁን ባለው መረጃ በአደጋው የ12 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡
7 ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ጠቁመው÷7 ሰዎች ደግሞ በዋና ከአደጋው መትረፋቸውን ገልጸዋል።
ማህበረሰቡ የተከዜ ወንዝ ግድቡ እስኪጠናቀቅ እንቅስቃሴውን በጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥትም በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሰሃላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጓዙ በደረሰ አደጋ ሕይዎታቸው ላጡ ወገኖች የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።