የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ልዑክ በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን አጽናና
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ልዑክ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የመሬት መንሸራተት አደጋ በተከሰተበት ቦታ በመገኘት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 85 ቶን የሰብዓዊ ድጋፍ አስረክቧል።
በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ፕሬዚዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ የተላከው ልዑክ በስፍራው ተገኝቶ በተፈጠረው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን አጽናንቷል፡፡
በዚህ ወቅትም በአደጋው የተጎዱትን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንደምትቆም የልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የ85 ቶን የሰብዓዊ ድጋፍ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን÷ ድጋፉ ቀጣይነት እንዳለው ተጠቁሟል።
በዚህም በዓይነት ለህጻናት እና ለሌሎችም ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የያዙ ድጋፎችን አድርገዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር)÷ መንግስት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡