ለውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት ማሻሻያ ስኬታማነት የተደረጉ ሰፊ ቅድመ ዝግጅቶች፡-
1. በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎም ወስኗል፡፡ በዚህ ረገድ፣ መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚጠቀሙባቸውን ነዳጅን፣ ማዳበሪያን፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይትን የመሳሳሉ ከውጭ የሚገቡ የአራት መሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ጫና በአንድ ጊዜ ወደ ሸማቹ እንዳይተላለፍ ወስኗል፡፡
2. ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት የእውነተኛ ገቢያቸው ዋጋ ለተሸረሸረባቸው ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ በዋጋ ንረት ምክንያት የደረሰውንና ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማርገብ ሲባል ያለውን የገንዘብ ምንጭ በመጠቀምና የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በማያባብስ መልኩ ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ዉደነት መደጎሚያ ደሞዝ ለመጨመር ታስቧል፡፡
እንዲሁም፣ በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የሚደረገው የሴፍቲኔት እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ የእነዚህ እርምጃዎች ዝርዝር አፈጻጸም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የሚገለጽ ይሆናል፡፡
3. የመንግሥትን የማህበራዊ ወጪ ለመደገፍና ሰውጭ ዕዳ ክፍያ የሚውለው ከፍተኛ የብር ወጪ ሌሎች ወጪዎችን በማይሻማ መልኩ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዳ የውጭ ዕዳ ማቅለያ እርዳታ ተገኝቷል፡፡ ይህን መሰል እርዳታ ቀደም ብሎ መገኘቱ መንግሥት ለማህበራዊና ድህነት ተኮር ወጪዎች የሚያውለው የሀብት አመዳደብ እንዳይስተጓጎልና በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳዋል፡፡
ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት የመፍትሔ እርምጃዎች ባሻገር፣ ወደ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ለማሳለጥና በገንዘብና በፊስካል ፖሊሲዎች መካከል ቅንጅት መኖሩን ለማረጋገጥ የብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡