የአፋር ክልል ም/ቤት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ለተያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል ከ12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ባለፉት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የክልሉ አስፈጻሚ አካላት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ጨምሮ የክልሉን ዋና ኦዲተርና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሪፖርት መርምሮ አጽድቋል፡፡
በምክር ቤቱ የዛሬ ውሎ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ መሃመድ÷የክልሉ የ2017 በጀት ዓመት 12 ቢሊየን 870 ሚሊየን 586 ሺህ 792 ብር በላይ ሆኖ እንዲጸድቅ ለም/ቤቱ አቅርበዋል፡፡
የረቂቅ በጀቱ ከክልሉ የውስጥ ገቢ፣ ከመንግስት ግምጃ ቤትና ተያያዥ የፋይናንስ ምንጮች የሚገኝ መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
ረቂቅ በጀቱ በክልሉ የህብረተሰቡን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ዘርፍ ለማሻሻል እንደሚውልም አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውስን የመንግስት ሃብትና በጀት ለታለመለት የልማት ሥራ በአግባቡ እንዲውል በማሳሰብ የቀረበውን ረቂቅ በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም የክልሉ ምክርቤት መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በዚህም መሰረት፡-
1. ወ/ሮ ኤይሻ ያሲን – የክልሉ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ
2. አቶ አህመድ አብዱቃድር – ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ
3. አቶ መሃመደ አሊ ቢኤዶ – የመንግሰት ኮሚዩኒኬሺን ቢሮ ሃላፊ
4. አቶ ኡሙርኑር አርባ – የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ
5. አቶ ኢብራሂም ሁመድ – ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ
6. አቶ ኢብራሂም መሀመድ – እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ
7. አቶ አህመድ ኢብራሂም – ወጣትና ባህል እስፖርት ቢሮ ሃላፊ
8. አቶ እስማኢል መሀመድ አሊ – ፍትህ ቢሮ ሃላፊ
9. አቶ ገዶሀሞሎ – በቢሮ ሃላፊ ደረጃ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ
10. ወ/ሮ ፋጡማ መሀመድ – የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ
11. አቶ ሳኒ መሀመድ – የአውሲ ረሱዞን ምክትል አስተዳዳሪ በመሆን እንዲሾሙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት መሰረት ምክር ቤቱ ሹመቱን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡