Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት አትቀበልም-አቶ ገዱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ሰበብ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚኖራትን ቀጣይ የመልማት መብት የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አረጋገጡ።
 
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በግድቡ የውሃ አሞላል ያደረጉት ድርድር በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ወደ ስምምነት ቢቃረቡም፤ ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች የሚያቀራርቡ ሐሳቦች ተቋርጧል።
 
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታደርገው ድርድር ግድቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች እንጂ በቀጣይ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ የመልማት መብቷን እንደማያካትት አቶ ገዱ ተናግረዋል።
 
ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገውን ድርድር በማስታከክ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የሚኖራትን መብት ለመገደብ እየሞከረች መሆኗንም አስረድተዋል።
 
የግድቡ ጉዳይ የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንድ ነጠላ አካል ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት መታየት ያለበት ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በተደራደሩበት የትብብር ስምምነት መሠረት ነው ብለዋል።
 
ስምምነቱ የወንዙን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ማዕከል ማድረጉን አስታውሰው፤ ግብፅ ከአሁኑ የሦስትዮሽ ድርድር አፈንግጣ መውጣቷን ገልጸዋል።
 
ስምምነቱን ከተደራደሩት 10 አገሮች ስድስቱ የፈረሙ ሲሆን፤ ከነዚህም ኢትየጵያን ጨምሮ አራት አገሮች ስምምነቱን በፓርላማቸው አፅድቀው የሕጋቸው አካል አድርገውታል።
 
በመሆኑም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ተጠቃሚነት በተመለከተው ስምምነት መሠረት ወንዙን በፍትሃዊነት መጠቀም ትችላለች ብለዋል አቶ ገዱ።
 
ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ድርድር ግድቡን ብቻ እንደሚመለከትና ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌላ ግድብ የመገንባትም ይሁን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወንዙን የመጠቀም መብቷን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
 
ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ መንግሥት ተቋማት በተናጠል የሚወጡ መግለጫዎች ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት አኳያ እንዴት ይታያል? ጥያቄ ለአቶ ገዱ ቀርቦላቸዋል።
 
“እንዲዚህ ዓይነት መግለጫ ባያወጡ ተመራጭ ነበር” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን ምንም ዓይነት ውጫዊም ይሁን ውስጣዊ ችግር ግድቡን ውሃ ከመሙላት እንደማያግዳት ተናግረዋል።
 
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.