በአፋር ክልል ሕገ-ወጥ ንግድ በፈጸሙ 748 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ሰሞኑን በንግድ ስርዓቱ ላይ ግብይቱን ባስተጓጓሉ 748 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ አደን ሂንከብ እንደገለፁት÷ መንግስት የወሰደውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ተከትሎ በገበያ ላይ ያልተገባ እንቅስቃሴ እንዳይታይ በክልል የተደራጀው ግብረ ሃይል በየደረጃው ባለው መዋቅር ጠንካራ ስራ እየሰራ ነው።
ግብረ ሃይሉ ባደረጋቸው የክትትል ሥራም አብዛኞቹ የክልሉ ከተሞች ላይ የተረጋጋ ግብይት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ሊሆን የቻለው ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሠራታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁንና አሁንም ያላቸውን ሸቀጥ የሚያሸሹና የሚደብቁ፣ ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩና ዋጋ ላይ ያልተገባ ጭማሪ የሚያደርጉ እንዳሉ በግብረ ሃይሉ መለየቱን ገልጸዋል።
በህጋዊ መንገድ ሥራቸውን ማካሄድ ሳይችሉ በቀሩ፣ ምርት በሸሸጉ እና በደበቁ 748 የንግድ ተቋማት ላይ ግብረ ሃይሉ የንግድ ተቋማቸውን የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 21ዱ የንግድ ፈቃዳቸው ጭምር እንዲታገድ መደረጉን አቶ አደን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡