Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ ቀናት ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ዝናብ ይኖራል- ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ 11 ቀናት የሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት የማስከተል አቅም ስለሚኖረው የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ፡፡

በዚህም በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምስራቅ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ጠንካራ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚፈጠረው ጠንካራ የደመና ክምችቶች ላይ በመነሳት በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜን ምስራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ ስፍራዎች ላይ በረዶና ነጎድጓድ የቀላቀለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ተብሏል፡፡

በመሆኑም የሚኖረው ተደጋጋሚነት ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የማስከተል አቅም ስለሚኖረው የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት 11 ቀናት ከትግራይ ክልል ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ እና ምዕራብ ዞኖች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ ዋግኽምራ፣ አዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፤ ከአፋር ክልል ቅልበቲ፣ ፈንቲ፣ አውሲ፣ ማሂ፣ ሃሪ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ማኦ ኮሞ እና ካማሺ ዞኖች፣ ከጋምቤላ ክልል ኑዌር፣ አኝዋክ፣ ማዣንግ እና የኢታንግ ልዩ ዞን ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፤ አዲስ አበባ፤ ድሬዳዋና ሐረሪ፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ፣ ስልጤ፣ የየም ዞኖች፣ ጠምባሮ፣ ቀቤና እና ማረቆ ልዩ ወረዳ፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ኮንታ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጋሞ፣ ጌዲኦ አማሮ እና ባስኬቶ ዞኖች፤ የሲዳማ ክልል ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ነው የተባለው፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተገለጹት አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ መላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ከኦሮሚያ ክልል ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፤ ከሶማሌ ክልል የሲቲ፣ ፋፈን፣ ኤረር፣ አካባቢዎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.