Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ከጅቡቲና ሩዋንዳ ጋር በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነት አዋጅን አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባውም የተለያዩ አጀንዳዎችን ተመልክቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ሹመትን የተመለከተ ሲሆን፥ በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የቀረቡለትን የተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን ለማሟላት አምስት አባላቶችን ሹመት አጽድቋል።

በዚህም መሰረት ሬቭናንድ ደረጀ ጀምበሩ፣ አቶ ደመላሽ ያደቴ፣ ዶክተር እዝራ አባተ፣ ወይዘሮ ፋጡማ ሀሴ እና ጋራድ ኩልሜ መሃመድ በተጓደሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን ምትክ ተሹመዋል።

ሹመታቸው የፀደቀው አምስቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

ምክር ቤቱ በመቀጠልም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።

በዚህም ረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን አዋጅን አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ ሪፐብሊክ መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነት እንዲሁም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችንም ተመልክቷል።

ረቂቅ አዋጆቹ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ ከጂቡቲ ሪፐብሊክ ጋር የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነት እንዲሁም በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በሩዋንዳ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነት በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጆችንም ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ከተወያየ በኋላም አፅድቋቸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የእቃዎች ሽያጭ ውሎች ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም የተመለከተው ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቆታል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የማዕድን ሥራዎች አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም የልዩ የመንግስት ዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅን ተመልክቶም ማጽደቁ ታውቋል።

በኢትዮጵያና በኳታር መንግስት መካከል የተፈረመውን የኢንቨስትመንት ማስፋፋት እና ጥበቃ ስምምነት ረቂቅ አዋጅን በኢትዮጵያ እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለበረሃ አንበጣ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም አጽድቋል።

እንዲሁም ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ እንዲያግዝ ለሁለተኛው የኢትዮጵያ የእድገትና ተወዳዳሪነት የልማት ፖሊሲ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ በኢትዮጵያ መንግስት እና በአለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ማጽቀዱ ነው የተገለፀው።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.