Fana: At a Speed of Life!

ለደቡብ ወሎ ዞን 30 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ለተለያዩ ወረዳዎች 30 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ደሴ ቅርንጫፍ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በመተባበር በደቡብ ወሎ ዞን ለተለያዩ ወረዳዎች ለሚገኙ ጤና ተቋማት 10 ሚሊየን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ተቋማቱ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ ቤቶችን ገንብተው ማስረከባቸው ተገልጿል፡፡

ለዚህም የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፉን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉ ነው የተመላከተው፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ÷ተቋማቱ ያደረጉት ድጋፍ በወሳኝ ጊዜ የደረሰና የጤና ተቋማቱን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ መላኩ ቸኮል በበኩላቸው ÷የተደረጉ ድጋፎች በጥናት የተለዩ መሆናቸውን ገልፀው ማህበሩ የተቸገሩትን የመርዳት ተግባሩ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡

ድጋፍ የተደረገላቸው የጤና ተቋማትና ማህበረሰቦችም የተደረገው ድጋፍ የሚታዩ እጥረቶችን የቀረፈና በአስፈላጊ ሰዓት የተገኘ ችግር ፈቺ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለክልሉ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችና ግብአት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የአልትራ ሳውንድ መሳሪያ፣ የማዋለጃ ማሽኖች፣ የወባ ህክምና ግብአቶች፣ ኦክስጅን ማምረቻ፣ የህጻናት ማሞቂያ ማሽኖች ጨምሮ ለሎች ግብአቶች የሚገኙበት ሲሆን፤ ለካማሽ ወረዳ እና ማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማጠናከር እንደሚውል የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ አመልክቷል።

 

በከድር መሃመድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.