Fana: At a Speed of Life!

ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት መጀመሩን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ የሚስተናገዱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ የፌዴራል ፖሊስ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ለአብነትም በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄዱ በርካታ ኮንፈረንሶች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቁ በትኩረትና በትብብር መሰራቱን አንስተዋል፡፡

በተመሳሳይ ለቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶች ሰላም እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲስተናገዱ ተገቢው ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል ጋር ዕቅድ በማዘጋጀት አስፈላጊው ዝግጅት መጀመሩን ነው ያስረዱት፡፡

እንግዶች ከሚያርፉባቸው ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

ሕብረተሰቡም በየትኛውም ሁኔታ ሕገ ወጥ እና አጠራጣሪ ድርጊቶችን ሲመለከት አቅርቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 እንዲሁም 46ኛው የህብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.