ዓለም አቀፍ የምልክት ቋንቋ ምርምር ጉባዔ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ዓለም ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ምርምር ጉባዔ እያስተናገደች ነው፡፡
ጉባዔው “የምልክት ቋንቋን መጠቀም ለመጭው ዘመን፤ መጭው ዘመንን የምልክት ቋንቋን በመጠቀም” በሚል መሪ ሀሳብ ለ15ኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው የሚገኘው፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባኤ ከመላው ዓለም የተውጣጡ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ የጉባዔው መካሄድ ለቋንቋውና ለዘርፉ አጥኚዎች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦችን ስርዓተ ትምህርት መቅረጽን ጨምሮ በሁሉም የህዝብ መገልገያ ዘርፎች ላይ አካታች የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ትልቅ ሚና ስትጫወት መቆየቷን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እንደመሆኑ በትብብር ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ በኢትዮጵያ ራሚስ አልካባሮቭ ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ይህን ጉባዔ ማዘጋጀቷ ለምልክት ቋንቋ ምን ያህል ትኩረት በመስጠት እየሰራች እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።
አክለውም የምልክት ቋንቋ አለመስፋፋት ጉዳቱ የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎችን ብቻ ሳይሆን የቋንቋው ተጠቃሚዎች ለሀገራቸው የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ጭምር መጉዳቱን ጠቅሰው፤ እያደገ በመጣው መነቃቃት የቋንቋው ተጠቃሚዎች ከምንጊዜውም በበለጠ በሁሉም መስክ እንዲሳተፉ በማድረግ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ይገባል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀው የምልክት ቋንቋ ትምህርትን በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ማህበረሰቡ በየቀኑ ሊጠቀመው ይገባል ብለዋል፡፡
በሰማኸኝ ንጋቱ