Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብትን በማስቀደም ሽብርተኝነትን መዋጋት እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሰብዓዊ መብትና ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ሽብርተኝነትን የሚያባብሱ መሰረታዊ ሁኔታዎችን እልባት መስጠት እንደሚገባም የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ አሳሰቡ።

ምክትል ዋና ፀሐፊዋ በፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በአሁኑ ወቅት ሽብርተኝነት በሁሉም መልኩ በአፍሪካ ሰላም፣ ደኅንነት እና ዘላቂ ልማት ላይ ትልቁን አደጋ እያስከተለ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።

በተለይም ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ በዓለም ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት 59 በመቶውን ይሸፍናሉ ብለዋል፡፡

በዚህም በሦስት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከሽብርተኝነት ጋር በተገናኘ በሰሐራ ቀጣና ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን÷ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚሞቱት ከግማሽ በላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የምዕራብ አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከባድ አደጋ ላይ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሸባሪ ቡድኖች ድሮንን ጨምሮ በላቁ ቴክኖሎጂዎች አቅማቸውን እያሳደጉ እንደ ፋይናንስ፣ የሰው ኃይልን ጨምሮ ዕውቀትን በመጋራት በመተባበር ላይ እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡

በዚህም ለሽብርተኝነት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰው፥ ለሰብዓዊ መብትና ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ሽብርተኝነትን ለሚያባብሱ መሰረታዊ ሁኔታዎች እልባት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ፣ የሰላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዮ በበኩላቸው÷ በፈረንጆቹ 2024 በአልጀርስ በሚገኘው የአፍሪካ ሕብረት የፀረ-ሽብርተኝነት ማዕከል ከ3 ሺህ 400 በላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ከ13 ሺህ 900 በላይ ሰዎች ሕይዎታቸው አልፏል ማለታቸውን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በዚህም አህጉራችን ትልቅ እና አሳሳቢ ፈተና እየተጋፈጠች ነው ፤ ሽብርተኝነትን ሁሉም በአንድነት ለመዋጋት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

በመሠረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.