Fana: At a Speed of Life!

ከለውጡ ወዲህ የተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚውን ከቀውስ ታድገዋል- አቶ አህመድ ሽዴ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት ገቢራዊ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ከቀውስ መታደግ ማስቻላቸውን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።

አቶ አህመድ ሽዴ በኢኮኖሚው መስክ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከለውጡ በፊት የመንግሥት ገቢ የተቀዛቀዘበት፣ የዕዳ ጫናው የናረበት፣ የባንኮች የማበደር አቅም ያሽቆለቆለበት በአጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ ያልሆነበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ችግሮችን ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ጤናማ ኢኮኖሚ በመገንባት ከቀውስ መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የፊሲካልና ሞነታሪ ፖሊሲ ርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሻሻያዎች፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድጉ አሰራሮች ገቢራዊ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባንኮች በኢኮኖሚው ላይ የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመንግሥት የተወሰዱ የፖሊሲ ርምጃዎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ገቢያቸውን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አፈጻጸማቸውን በማሻሻል ኢኮኖሚው እንዲያገግም ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ የትይዩ ዋጋው ከመደበኛው ጋር እንዲቀራረብ ከማስቻሉም በላይ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ነዳጅን ጨምሮ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ መደረጉን ገልጸው፤ መንግሥት ባደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.