ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ሲያከብር የኮቪድ19 መከላከያ መንገዶችን እና የተቀመጡ ክልከላዎችን በመተግበር ሊሆን ይገባል – የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በእምነቱ የተቀመጡ የወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ተግባራዊ በማድረግ መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እንድሪስ በዓሉን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ሙስሊሙ ማህበረሰብም ይሁን ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎች ኮሮናን በመከላከል ረገድ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የዘንድሮውን የአረፋ በዓል የምናከብረው እንደ ቀደሙት አመታት በአንድ ላይ ተሰባስበን ሳይሆን ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን በመከወን መሆን ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡
ሙስሊሙ ማህበረሰብ በአረፋ በዓል ላይ የተቸገሩትን በመርዳትና የታመሙትን በመጠየቅ ሰብአዊ ተግባር እንዲፈጽምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም ሰብአዊነትን በተግባር በማሳየት እና ሙስሊሙ ማህበረሰብ በያለበት ቦታ ሁሉ የዱዓ ፀሎት በማድረግ በአሉን እንዲያከብርም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ እንኳን ለ1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
1 ሺህ 441ኛው የአረፋ በዓል ከነገ በስቲያ አርብ የሚከበር ይሆናል፡፡
በሙሀመድ አሊ