የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሕዝቡ የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዴሞክራሲ ተቋማት በራሳቸው አዋጅ የሚተዳደሩበትንና በገለልተኝነት የሚሰሩበት እድል መፈጠሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ ገልጸዋል።
ተቋሙ ህገ መንግሥታዊ እና ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ያነሱት ዋና ዕንባ ጠባቂዋ፤ ሰራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን አይችሉም ብለዋል።
በዚህም በአስፈፃሚ አካላት የሚደርሱ ቅሬታዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ አንስተዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማት በራሳቸው አዋጅ እንዲተዳደሩ፣ ሥራቸውን ነፃና ገለልተኛ ሆነው ማከናወን እንዲችሉ በማድረግ ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ መንግሥት ሚናውን እንደተወጣ ጠቁመዋል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መንግሥትና ሕዝብ የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው÷ ሕዝቡ የተቋሙን ኃላፊነት በውል ተገንዝቦ ሊገለገልበት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሰረት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ህገ መንግስታዊ የዴሞክራሲ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡