ብልጽግና ፓርቲ የልማት ሥራዎች የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚያጎላ አግባብ እየተከናወኑ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚያጎላ አግባብ ታቅደው እየተከናወኑ መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ፡፡
ፓርቲው ለዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስላተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም፤ ሴቶች ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌላው ማሕበረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠር እና በትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሳተፍ ችለዋል ብሏል፡፡
ፓርቲው ለዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ያስተላለፈው የእንኳ አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧ፡-
እንኳን ለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለሀገር ብልፅግና መሰረት ነው፡፡
የፓርቲያችን ፕሮገራም ሴቶች በሚደርስባቸው ሁለንተናዊ ጭቆና ምክንያት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸው በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን ይገነዘባል።
በመሆኑም የሴቶችን ፍትሐዊ የፖለቲካ ውክልናና ተሳትፎ እንዲሁም ዘላቂ የሥራ ዕድል፤ የብድር አቅርቦት፣ የመሬት ባለቤትነት፣ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚነት እና ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ እንዲያገኙ እያደረገ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
በዋናነትም የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ በማደራጀት፣ እርስ በርስ ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግቧል።
በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ እምብዛም ከነበረበት፤ ፓርቲያችን በሰጠው ልዩ ትኩረት በአሁን ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እስከ 50 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡
በፖለቲካ ተሳትፎና በአመራርነት ብቃታቸው ምሳሌ የሆኑ ሴቶችን በማብቃት ፓርቲው የአርአያነት ሚና ተጫውቷል።
በዚህም ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ በማድረግ በተሰማሩበት የሥራ መስክና የአመራር ሰጪነት ቦታ ተግባራቸውን በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ማየት ተችሏል፡፡
ጠንካራና ቅቡልነት ያለውን ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ፤ የሴቶች ሚና የጎላ እንዲሆን ፓርቲው አበክሮ በመሥራቱ የሴቶች ተሳትፎ እየጎለበተ መጥቷል።
የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልማት እና በህብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ራሳቸውን በገቢ እንዲያሳድጉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
ሴቶች ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌላው ማሕበረሰብ የሥራ ዕድል መፍጠር እና በትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሳተፍ ችለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የሴቶችን ተጠቃሚነት በሚያጎላ አግባብ ታቅደው እየተከናወኑ ናቸው፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ሴቶችን ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የተጀመሩ የልማት ተግባራት ለውጤት እንዲበቁ በሌማት ትሩፋትና በሌሎችም የልማት ተግባራት ሴቶችን በማሳተፍ እምርታዊ ውጤቶችን አስመዝግቧል።
ሴቶች በሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በማጉላት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ በመቻሉ የሰላም አምባሳደርነታቸውን አስመስክረዋል።
ፓርቲያችን የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ዘርፍ ማረጋገጥ ሲቻል፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው አጠቃላይ የሪፎርም ሥራዎች እንደሚሳኩ ፅኑ እምነት ስላለው የሀገራችን ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበክሮ እየሰራ ውጤትም እያስመዘገበ ነው።
ዛሬ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ስናከብር የሀገራችንን ሴቶች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ከዳር ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናችንን በማጉላት መሆን ይገባል።