ምሁር ኢ-ምክንያታዊና አድሏዊ እሳቤዎችን ለማረቅ መስራት አለበት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምሁር አድሏዊ እና ኢ-ምክንያታዊ እሳቤዎችን ለማረቅና ለማስተካከል በትኩረት መስራት አለበት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክተው “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
በጽሑፋቸውም በምሁርነት ውስጥ እንቅፋቶች አሉ፤ ከእነዚህ ውስጥም ስሜታዊነት አንዱ ነው፤ ምሁር ማለት ግን የስሜት ህዋሳቶቹን ተጠቅሞ መረጃን የሚሰበስብ እንጂ ስሜታዊ የሚሆን አይደለም ብለዋል፡፡
አድሏዊ እሳቤዎችን እና ኢ-ምክንያታዊ የሚያደርጉ ባህሪያትን ምሁር ከራሱ እንደሚያርቅ ገልጸው ÷ ቡድንተኝነት ደግሞ ሌላኛው እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሰው በግሉ ነው ማሰብ ያለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷በግል የማሰብ አቅምን የሚገዳደር ነገር እንዳይኖር ምሁራን ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከእውነት ይልቅ ከሌሎች ጋር መመሳሰል እና ለምን የሚል ጥያቄን መጠየቅ አለመቻል የምሁርነት አንዱ ተግዳሮት እንደሆነ አብራርተዋል።
ርዕዮት እና ቀኖናዊነት ሌላኛው እንቅፋት መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም አዲስ ነገር ለመመልከት ዝግጁ አለመሆን ማለት እንደሆነ አመልክተዋል።
የመግለጫ ጎርፍና ጫጫታ እንዲሁም ትዕቢትና ማናለብኝነት ሌሎቹ በምሁርነት ውስጥ የሚገኙ እንቅፋቶች ናቸው፤ ስለሆነም እነዚህን ተግዳሮቶች ማስወገድ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ምሁራን ቅድመ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን፣ አብዮታውያን ምሁራን ፣ስደተኞቹ ምሁራን እና ተስፈኞቹ ምሁራን በሚል በአምስት መደብ እንደሚከፈሉ አስረድተዋል።
ቅድመ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን የሚባሉት የእውቀት ገበያቸው የአብነት ት/ቤት፣ መድረሳዎች እንደሆኑና የእውቅት ዘርፎቻቸውም ሕግ፣ ፍትሃ ነገስት፣ ስነ መለኮት፣ ቅኔና ፍልስፍ ነው፤ ለአብነትም ዘርዓያዕቆብን ጠቅሰዋል፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን የምንላቸው ደግሞ በመደመር መንግሥት የወግ አጥባቂው ትውልድ ተብለው የሚታዩና በባህርማዶ ትምህርት የቀመሱ ናቸው ፤ ለእነዚህም ነጋ አድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝና ሃኪም ወርቅነህን ለምሳሌነት አንስተዋል።
ግርማሜ ነዋይ፣ ሃይሌ ፊዳ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ እና ተስፋዬ ደበሳይ ደግሞ በሶስተኛው የአብዮታውያኑ ምሁራን የሚካተቱ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
አራተኛዎቹ ስደተኛው ምሁራን ለትምህርት ሄደው እዛው የቀሩ መሆናቸውንና በዚህ መደብ ውስጥ ካሉት ምሁራን መካከልም ገቢሳ ኤጀታ (ፕ/ር) እና ሃይሌ ገሪማን (ፕ/ር) ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ተስፈኞቹ ምሁራን ደግሞ የውጭ ትምህርት እድልን አግኝተው ተምረው ነገር ግን ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንግልትን ያዩ የሀገራቸውን የወደፊት ተስፋ አርቀው የሚያዩ ናቸው ነው ያሉት ።
ከእነዚህ መካከልም በየነ ጴጥሮስ ((ፕ/ር)፣ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) እና መስፍን ወ/ማሪያም (ፕ/ር) እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ