የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሠራን ነው- አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝባችን የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ የሲዳማ ሕዝብን ከወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት፤ በ2016 ዓ.ም ክረምት ወቅት የፌዴራል ተቋማት በሕዝብ ውክልና ሥራ ለተነሱ ጥያቄዎች ከተለያዩ ሚኒስቴሮች የተሰጡ ምላሾችን የምክር ቤቱ አባላት ማቅረባቸው ተጠቅሷል፡፡
ከተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ከመሠረተ-ልማት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ለተለያዩ ሚኒስቴሮች መቅረባቸውም ተገልጿል።
በክልሉ ሁሉም የምርጫ ክልሎች ከሕብረተሰቡ ለሲዳማ ክልል መንግሥት የተነሱ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ አባላት መቅረባቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በሰጡት ገለጻ፤ የፌዴራል ተቋማት ከሰጡት ምላሽ ባሻገር የክልሉ መንግሥት በአጭርና ረዥም ጊዜ አቅዶ የሚሠራቸውና የሠራቸው በርካታ መሠረተ-ልማቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሕዝባችን የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡