Fana: At a Speed of Life!

ደሴን ጨምሮ በዙሪያዋ ባሉ ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም ላይ የሠዓት ለውጥ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እስከ ረመዳን ፆም መፍቻ ድረስ በደሴ ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ወረዳዎች የሚገኙ የከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚዎች ከቀኑ 10 ሠዓት እስከ ምሽቱ 3 ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙ ተደረገ፡፡

ይህ የተደረገው ከዚህ በፊት የደሴ 66 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ከዐቅም በላይ የሆነ የኃይል ጭነት ያለበት በመሆኑ እና በረመዳን ፆም በተለይ ከቀኑ 10 ሠዓት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የኃይል ጭነት እያስተናገደ ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም በአካባቢው የሚገኘው ሕብረተሰብ ፆሙን ያለኤሌክትሪክ መቆራረጥ በሰላም እንዲያሳልፍ ለማስቻል ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ወፍጮ ቤቶች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ እንጨትና ብረታ ብረት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎች ከትናንት ጀምሮ እስከ ረመዳን ፆም መፍቻ ድረስ ከቀኑ 10 ሠዓት እስከ ምሽት 3 ሠዓት ተለዋጭ የኃይል አማራጭ እንዲጠቀሙ መደረጉ ተገልጿል፡፡

እነዚህ ደንበኞች እስከ ቀኑ 10 ሠዓት እንዲሁም ከምሽት 3 ሠዓት በኋላ መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም እንደሚችሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ሪጅን ዳይሬክተር ሀብቱ አበበ ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

ይህንን ተገንዝበው ደንበኞቹ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የጠየቁት ዳይሬክተሩ፤  ለተፈጠረው የአገልግሎት መስተጓጎልም ደንበኞቹን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ይህ የሠዓት አጠቃቀም ተግባራዊ የተደረገው በደሴ ከተማ እንዲሁም በወረባቦ፣ በሐይቅ፣ በውጫሌ፣ በአልብኮ፣ በኩታበር ወረዳዎችና አካባቢዎቻቸው ባሉ የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.