Fana: At a Speed of Life!

የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ አፈፃፀም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2017 በጀት ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ የማጓጓዝ አፈፃፀም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝ የተቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴ ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡

በዚህም እስከ መጋቢት 4 ቀን ያለው አፈጻፀም የተገመገመ ሲሆን፤ በዓመቱ ከተያዘው 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ውስጥ ከ700 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ ሀገር ውስጥ ማጓጓዝ ተችሏል ተብሏል፡፡

የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የታየው አፈፃፀም እና በተቋማት መካከል የነበረው መናበብ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

አፈፃፀሙ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ከተያዘው የግዥ ዕቅድ ጋር እጅግ የተጣጣመ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ የስትሪንግ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፤ ወደ ሀገር ውስጥ ያልገባውን ቀሪ ማዳበሪያ በፍጥነት አጓጉዞ ለማጠናቀቅ የታየውን ቅንጂታዊ አሠራር ማጠናከር እንደሚገባ መገለጹን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ለዚህም አማራጭ ወደብን መጠቀም እና የጂቡቲ ወደብ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ማሳደግ እንዲሁም ባቡርን ጨምሮ የተሸከርካሪ አቅርቦቱን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.