የኢትዮ-አሜሪካን ዘርፈ-ብዙ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና አሜሪካን ኢኮኖሚያዊ ጨምሮ ዘርፈ-ብዙ ትብብሮች በይልጥ ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተካሄደ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ የአፍሪካ ፖሊሲ ከፍተኛ ፕሮፌሽናል ስታፍ አባል ከሆኑት ጆን ቶማስዘውስኪ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅትም፤ በኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነት ላይ ያሉ ትብብሮችን በይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትብብር በይበልጥ የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ሚኒስትር ዴዔታዋ አስረድተዋል፡፡
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ቁልፍ አጋሯ መሆኗንም በውይይቱ ወቅት አስረድተዋል፡፡
ጆን ቶማስዘውስኪ በበኩላቸው፤ በአሜሪካ መንግሥት አሥተዳደር ውስጥ ያሉትን ለጋራ ተጠቃሚነት እና ዕድገት ምቹ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦች አብራርተዋል፡፡
ያሉትን ዘርፈ-ብዙ ትብብሮች ለማጠናከር እና ተጨማሪ ዕድሎችን ለማመቻቸትም ቀጣይነት ያለው ምክክር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡